ደገኛው

በርኖስና ባና፣ ኩታና ጋቢውን፣

ደገኛ እሚለበሰው፡ ነበር ዕድሜ ልኩን ፡፡

​ሸማኔው ዘንድሮ፣ ጭዱን እያሳሳው፣

ይበታተን ገባ፣ መንፈቅም ሳይሞላው።

አላውቂ ሳሚ በፈጠረው ችግር

ቆዳው ይጠወልግ፡ ይኮማተር ጀመር።

 

ሙቀቱና ብርዱ ሲፈራረቁብን

መሞቁም መኖሩም አላምርብን ብሎን

በነጋ በጠባ ሲቀንስ ቁጥራችን

ተጠራርገን ሳናልቅ ሳይጠፋ ዘራችን

በቁም ከመቃጠል ሰለማይብስብን

አማረ አላማረ ጥርሳችንን ነክሰን

በደቦ ለመሥራት መቀናጀት ይዘን

በተናጠል ኑሮ መጣመኑን ትተን

እንመክት ጠንክረን

እንሥራ ተባብረን

ዳጎስ ወፈር ይበል ኩታችን ጋቢያችን

በርኖስ ዝተታችን

ወደነበረበት ይመለስ ክብራችን።