አዬ ሸማ ደጉ

 

ሲዋጥ በመረቅ ነው፣ አዳም መሳሳትህ፣

በለስ ባትበላ፣ ህገወጥ ሆነህ፣

ዕርቃን ቀርቶ ነበር፣ ዘርህ ዘር ማንዘርህ።

 

ዛሬ ሰው ሁሉ፣ ሰው መስሎ እሚታየው፣

የውስጡን ገመና፣ በልብስ አጅሎ ነው።

 

ዳዴ እያልሽ ኑሪ፣ እባብ እድሜ ይስጥሽ፣

ባዳም ጸደቅሽበት፣ ሔዋንን አስተሽ።

ዕፀ በለስ ቀምሶ፣ ባይከፍትማ ዓይኖቹን፣

እያለ ሳያየው፣ ይኖር ነበር ነውሩን።

 

ዓይኑ ሲገለጥ ግን፣

በቅጠል መከለል፣ አልበቃው አለና፣

ጥጥ ፈትሎ ሽምኖ፣ ሸፈነ ገመና!

 

አዬ ሸማ ደጉ፣ እየሸፋፈነው፣

አውሬነቱን ጋርዶ፣ ሰውን ሰው አሰኘው።