ቀና ደፋ

 

ሲሠራ ሲበላ፡ ካገር ልጅ ከዘመድ

ባገሩ ነበረ ሰው ኮርቶ እሚራመድ።

አገሩ ያጣውን

ሰብአዊ ክብሩን

እንደማያገኘው ካጥናፍ አጥናፍ ቢዞር

ቀድሞ ቢያውቀው ኖሮ መች ይሰደድ ነበር፤

ለቀውጢ ደላላ ሳንቲሙን አራግፎ

ባሸዋ በባህር ከመበላት ተርፎ

ደላላው እንዳለው

ክሰማይ ላይ ወተት የምታዘንበውን

የህልም እንጀራውን

ባልገነባው ‘ህንጻ’ የምታኖረውን

ያልሠራበት ‘ደሞዝ’ የምትከፍለውን

ቀልማዳ ደላላ - ግን ያልነገረውን

በ’መልስ’ ጥበቃ ሲባንን ቀን ተሌት

 እንዲያይ መሬት መሬት

አስዋሽታ አስቀላምዳ

አድቅቃ አሽመድምዳ

ደም እንባ አስለቅሳ

ውሎ አድሮ ውሎ አድሮ

ደጋግሞ  ውሎ አድሮ

ሕይወቱን አክርማ ከብሩን አሸማቃ

መልሱ ሲመጣለት ጥበቃው ሲበቃ

ጉዳይ የማይሞላ ሆኖ ሰባራቃ

የምታደርገውን

የተደፋ አንገቱን የምትሰብረውን

የንግልጣርን መሬት ደርሶ እስኪኖርባት

በተራቡ ዓይኖቹ ከርቀት እያያት

ለጊዜው ማራረፊያ

በባህሩ ዳርቻ በፈረንሳይ ምድር

በ ‘ካሌ’ አካባቢ የቀለሰው ጎጆ

ቡልዶዘር ገባበት ‘ጀንግሉ’ ፈረሰ፡

ላሟም እልታለበች:  ሀልሙም አልደረሰ።

                ***

ድንቄም ተኖረና ‘ውጣ!’ ተባለሳ!

ጓዝ ጓዙን ቋጥሮ አዳሜ ተነሳ

ተነግሮታልና ቢውል እንዳያደድር

ሂድ ወዳሉት ቦታ ይዥጎደጎድ ጀመር።

ካሰበው ሳይደርስ ሰው መቼ ያቆማል፡

ትንፋሹ እስከሚቆም በተስፋ ተሞልቶ

ግፋኙን ወደፊት ወደፊት ይጓዛል

ነገን ለመጨበጥ ቀና ደፋ ይላል!

ዋ! ይብላኝ አሞራው!

ደጋግሞ መነቀል፡ ደጋግሞ መፈንቀል!!!

ዓለም ዳኛ የላት ለማን ‘አቤት ይሏል፡

ሆድ ይፍጀው እያሉ

ጨጓራን መላጥ ነው፡ እንጀትን ማቃጠል

እየተቃጠሉም መታገል ለመጣል።

 

ለ ‘ካሌ ኤክሶደስ’ መሪር ትዝታ

 

(In repugnant memory of the starting of the demolition of ‘The Jungle’ Camp in Calais (France) and the Exodus of its around 10,000 occupants, migrants, on Monday 24 October 2016)

 

Camp’ Follow up 26 10 2020