እሱም አልነገረኝ!

የሰሜን ተራሮች ድምቀትና ውበት፣

በዝናብ ሹል እርሳስ በጎርፍ ሳይነት፣

የወንዝ የዱሎሎ፣ ቅርጽና ደም ግባት፣

እፍ ተብሎበት፤

ተኩሎ ተሠርቶ፣ በተፈጥሮ ትጋት፣

ባገሬ መሬት ላይ፣ ተንጣሎ በስፋት፤

መኖሩን ሰምቼ፣ ከኔ ቀድመው ካዩት፤

እኔም በቃሁና፣ ለምሥክርነት፣

‘ቱሪስት’ ሆንኩና፣

በሰማይ ላይ ባቡር፣ እያቆራረጥኩት፣

ከሰማይ ጥግ ሆኜ፣ አሽቆልቁዬ አየሁት።

 

በጀርባዋ አዝላ፣ የውሃ እንስራዋን፤

ተተኪዋን ጋሜ፣ ነገ እምትወርሳትን፣

አሳዝላ ገንቦ፣ ሲጓዙ ጎንለጎን፣

አቀበት ለመውጣት፣ የሚዳክሩትን፤

ከልታማዋን እናት፣ የትዳር ዋልታዋን፤

ከሲታ የሆኑ፣ጠምዶ በሬዎቹን፣

በየጥጋጥጉ፣ በየጉራንጉሩ፣

ከነ ‘መቻል’ ጋራ፣ ችሎ ራብ ጥማቱን፣

በፍኝ ቆሎ ምሳ፣ ከማሳ ዋይውን፣

ቀንና አፈር ገፊ፣ አራሽ ገበሬውን፣

ፍየል ጠባቂውን፣

ትንሹ ማሙሽን፣

ገበያ ቀን ኖሮ፣ ያለውን ሻሽጦ፣

የሌለውን ገዝቶ፣ ወይንም ተለዋውጦ፣

ባህያው፣ በጀርባው በጉያው ሸጉጦ፤

በየጎዳናው ላይ፣ የሚኳትነውን፣

ባጋሰስ ባህያ ጫጭኖ ሸቀጡን፣

አጋሙን ቁልቋሉን፣

እባብ እፉኝቱን፣

ሌባ ቀማኛውን፣

ዳገት ቁልቁለቱን፣

ሁሉ ተቋቁሞ ሊያቋቁም ጎጆውን፣

የሚታትረውን፣

ሻጭና ገዢውን የሚያገናኘውን፣

ባዝኖ አደር ነጋዴ ጠንካራ ድልድዩን፤

ቄሱን ደብተራውን፣

ለጸሎት ለፍታት፣

ካንዱ ደብር፡ አንዱ ደብር፣ ሲጓዝ ነዋሪውን፤

እንዲያው በጠቃላይ፣ ያገር ነዋሪውን፣

እንዴት ያየው እንደሁ፣ እኔ ውብ ያልኩትን፤

ምን ያስብ እንደሆን፣

እኔም ሳልጠይቀው፣ ወይ እሱ ሳይነግረኝ፣

እንደ ‘ቱሪስቶቹ’፣ ያፍ ልማድ ሆኖብኝ፣

“አሜዚንግ” እያልኩኝ፣

‘ድንቅ ነው’ እያልኩኝ፣

ውስጥ ውስጤን ግን ንዴት እያንገበገበኝ።

በነበረበቱ ጥዬው ተመለስኩኝ።

ጉልበቴን ላባዳ ስገብር ኖርኩና፣

ዛሬ በስተርጅና፣

ሰው ያረገው ነገር፣ አይቅርብኝ ብዬ፣

ውበት ላደንቅ መጣሁ ‘ፈረንጅ’ መስዬ።

 

 

ባፍላነት ዘመኔ፣

ምኞቴን ጉጉቴን፣ የማሟላበትን፣

ሕልሜን ተከትዬ፣  

ውድ አገሬን ጥዬ፣

ካገር አገር ስዞር፣

ጉልበቴን ላባዳ፣ በከንቱ ስገብር፣

ወዶ ገባ ሆኜ፣ ያባከንኩት ህይወት፣

“ከጉርሼ ቀንሼ፣ ፊደል ያስቆጠርኩህ፣

የት ነበርክ ልጄ፣ አላውቅም አይቼህ!”

ያም አልበቃ ብሎህ፣ በብዙ ዘመንህ፣

እግር ጥሎህ መጥተህ፣ እንደ ባዳ ሆነህ፣

‘አንዴት ነህ?’ ሳትለኝ ዝም ብለህ ታልፋለህ?”

የሚል ልዩ መልዕክት፣

በኒህ ተራሮች ላይ፣

በጎልህ ተጽፎ፣ ሲወቅሰኝ አየሁት።

ራሴን ጠላሁት፣

ወኔዬን ጠላሁት፣

አገሬን ኣስትቶ፣ ያስኬደኝን ነገር፣ ሰበቤን ጠላሁት፣

ባንድ ሳር መመዘዝ፣ ባያፈስም ሳር ቤት፣

አስተዋፅዖ አለኝ፣ ቁጥሩን ለማብዛት።

ይኸንን እያሰብኩ፣

እንደተቆጡት ልጅ፣ ‘አርፈህ ቁጭ!’ እንዳሉት፣

ከልታማ ወገኔን በሩቁ እያየሁት፣

ቀልቤ እየፈለገ፣ ልለው ‘ይቅር በለኝ!’፣

እኔ ከላይ ሆኜ ፣አሱ  ከታች ሲያየኝ፣

አፌ ተለጉሞ፣ አንድም ቃል ሳይወጣኝ፣

አንደትናንትናው፣

ደግሜ እንዳልረሳው፣

ዛሬ ያየሁትን፣ ነገ አንዲያስታውሰኝ፤

ካሜራ ደግኜ፣ ዙሪያዬን የሚቃኝ፣

ላይ ላዩን አይቼ፣

እንደውርስ ሰነድ፣ ፎቶ ኮፒ አንስቼ፣

ሊፈታው ከቻለ፣ ውስጡን ለቄስ ትቼ፣

ፀፀት እንደቆሎ፣ እየቆረጠመኝ፤

በላይ አንደመጣሁ፣ በላይ ተመለስኩኝ።

 

ዐይታችሁ ሰምታችሁ፣ ይመስላችሁ እንደሁ፣

ለኔ እንደመሰለኝ፣

ሌላው እንደሚያደርግ፣ ሌላው እንደሚመኝ፣

ይኸን ያን ለማድረግ፣ ታስቡ እንደሆነ፣

የባህር ማዶ ድጥ፣ እንደኔ አሟልጧችሁ፣

ወድቃችሁ ሳትቀሩ፣

ዋይ ነዶ! ሳትሉ፣ ቀኑ መሽቶባችሁ፤

ትመኙ እንደሆነ፡ ለዚች ላገራችሁ፣

አንድ ጭብጥ ፍሬ በላይዋ ዘርታችሁ፣

ሲያፈራ ለማየት፣ በድሜ ዘመናችሁ፣

ትመኙ እንደሆነ፣

የተቀበልኩትን ከኢትዮጵያ እናታችሁ፣

ያደራ ደብዳቤ ግልባጭ፣ እንካችሁ፤

“በገጸ ምድር ላይ፣ እንደ አሸዋ ሁሉ የተበተናችሁ፣

የጉጉት ልጆቼ፣ የምናፍቃችሁ፣

በድሜ ለመሰንበት ዕድል ካገኛችሁ፣

ከያላችሁበት፣ ሰብሰብ ብላችሁ፣

ክውስጥም ከውጭም፣ ደሜን የሚመጡኝ፣

መሠሪ ጠላቶች፣

በቁሜ ሳይቀብሩኝ፣ ሳልሞት እናታችሁ!

 ‘አለን!’ በሉኝ ኑና፣ ኋላ እንዳይቆጫችሁ።