ፍቅር ነው ቋንቋዬ

 

ፊቴን የሚያፈካው

ውስጤን የሚያሞቀው

ኩታ ቡሉኮዬ፣ ያምላኬ ፍቅር ነው።

አንተ በሠራኸው፣ ባነጽከው አንደበት፣

አንተ በሰጠኸኝ፣ ቋንቋየና ቃላት፣

የፍቅርን ፍቅር፣

ባፌ ላንጎራጉር፣

በቃላት ልደርድር።

ብዘፍን ብዘምር፣ ሁሌም የማልመው፣

ትዘዝክን መፈጸም፣ ፍቅርህን መዝራት ነው!

ፊቴ የሚፈካው

ውስጤ የሚሞቀው

እንዳምላኬ ትዛዝ፣ በፍቅር ስኖር ነው።

ክፋትና ክፉ፣ ሳያልፉ በደጄ፣

በሰው ላብ በስው ደም፣ ሳይጎዳድፍ እጄ፣

መልካም ብቻ አስቤ፣ መልካሙን ፈጽሜ፣

በሠላም መኖር ነው ምኞቴና ህልሜ።

ፊቴ የሚፈካው

ውስጤ የሚሞቀው

ስጠራው ‘አቤት!’ ባይ፣ አምላክ ስላለኝ ነው።

ጆሮዎቼን ከልል፣ አንዳይሰሙ ክፉ፣

ጋርዳቸው ዐይኖቼን፣ እንዳይመርጡ ክፉ፣

ምርጫ የሰጠኸኝ፣ የፍቅር ባለቤት፣

ደግ አልሜ እንዳደርግ፣ ባርከው የኔን ጥረት።

ፌቴ የሚፈካው

ውስጤ የሚሞቀው

ፈቅርህን ወርሼ፣ ፍቅር ስዘራ ነው።

እኔ አገር የለኝም ዓለም ነው አገሬ፣

ሌላ ዘር የለኝም፣ የሰው ልጅ ነው ዘሬ፣

በሕይወት እስካለሁ መነጋገሪያዬ፣

አፍ የፈታሁበት ፍቅር ነው ቋንቋዬ።

ፊቴ የሚፈካው

ውስጤ የሚሞቀው

ፍቅርን ዘርቼ ፍቅር ሳመርት ነው።

በራስ መውደድ ስሜት፣ የታመሰ መንፈስ፣

አምላክ ሆይ በፀጋህ፣ በፍቅር ይታደስ።

ፈቃድህ ይፈጸም በምድር እንደሰማይ፤

ከጀንበር መውጣት ጋር፣ ሠላም ሲወጣ አንይ!

የሰው ልጅ ካነፀ፣ በፍቅር ላይ ቤቱን፣

አምላክ ይቅር ይላል፣ ይመልሳል ፊቱን።

እንደመሸ አይቀርም፣ ሌሊቱ ይነጋል፣

ብሩህ የሠላም ጎሕ፣ ሲቀድ ይታየኛል።