ሽንኩርቱ

ባልተወለደ አንጀት፣ በስለታም ቢላ፣

ሽንኩርት ከትፌ፣

አሽቼ አቁላልቼ፣

ወጥ ብጤ ሠርቼ፣

በቃኝን የማያውቅ፣ ቀፈቴን ልሞላ፣

ሆዴን እንጂ ሕመሙን፣

ሳልገምት ሥቃዩን፣

ገና ስጀማምር፣ ለመግፈፍ ቆዳውን፣

መዘላበድ ሰምቶ፣ ያላፊ አግዳሚውን፣

የ ‘አልሞት ተጋዳይ’ መከላከያውን፣

ዐይን የሚቆጠቁጥ፣ መርዙን ቢረጭብኝ ፤

‘ተደፈርኩ’ ብዬ ቡራከረዩ! አልኩኝ።

እልህ አሰከረኝ!

ባንድ እጄ አይበሉባ፣ ዕንባዬን እንትኔን እየጠራረግሁኝ፣

መሣሪያ ያኮራል፣

ቡከን ያጀግናል፣

እኔም ጀግና ሆኜ፣ ደካማ እማጉላላ፣

በተሳለው ቢላ፣

በታትኜ ጣልኩት፣ አንጀቴን አራስኩኝ።

እስክሰፈር ድረስ፣ በሠፈርኩት ቁና፣

ግና መቼ በቃኝ፣

ዛሬም እልጣለሁ፣ እከትፋለሁ ገና!!I