የሞኝ እንጉርጉሮ!

 

ምኞት ካልተሟላ፣
ኑሮን ካልለወጠው፣
ቢመጣስ ቢቀርስ፣
ሌላ ዓመት ምንድነው?
የዘንድሮው ዓመት፣ ላለም ለዘላለም፣
እንዳለ ቢወዘፍ እኔ ግድ የለኝም፤
አይለወጥ ቀኑ፣ በወና ጎጆዬ፣
ለሁልጊዜም ልኑር፣ ነገን ዛሬ ብዬ!
መስከረም አይጥባ፣ መስቀል አይተኮስ፣
ኅዳር ሳይታጠን፣ የምፅአት ቀን ይድረስ።
ዓለም ምጥ ይያዛት፣
ታስወርድ፣ ደም ይምታት፣
አዶ ከብሬ ለክፎ፣ ያግዝፍ ያስለፍልፋት፣
የምፅዓት ቀን ይሁን፣ ያለሁበት ሰዓት፣
ይደበላለቁ፣ መዐልትና ሌሊት
ለቅን ሰው ካልሆነች እውነት ካልተስማማት፡
ያረገዘችው ሸር፣ ሲጥ አርጎ ይግደላት።
ከብዙው ዋትቶ አደር፣ ጣዕሟን ደብቃ፡
ጥሩውን ምቹውን፣ ለጥቂት ሞሽላቃ፣
ያላንዳች ይሉኝታ፣ ያለምንም ሀፍረት፤
ጠቅልላ ስታጎርስ፣ ስትሰጥ እያየሁዋት፣
ጨሼያለሁ በንዴት!
እምዬ እኩልነት፤
ተጽፈሽ፣ አንብቤሽ፣
ተነግረሽ፣ ሰምቼሽ፣
አለች ባሉኝ አገር፣
በምሥራቅ በምዕራብ፣
በሰሜን በደቡብ፣
ትኖሪያለሽ ብዬ፤
እግሬ እስከሚነቃ፣ ስኳትን ላገኝሽ፣
ባራቱም ማዕዘን፣ ስባዝን ከርሜ፣
ዛሬስ ተስፋ ቆረጥኩ፣ ቅዠት ሆነ ሕልሜ!
እንደውሀ መውቀጥ፣
እዚያው እንቦጭ እንቦጭ፣ ከሆነ ውጤቱ፣
ኑሮን ከልለወጠው፤
ቢመጣስ ባይመጣ፣ ሌላ ዓመት ምንድነው?
ዳኛው ያለጉቦ፣ ካልተፈታ ፊቱ፣
ዕውነቱ ካልታየው፣ ቢደቀን ከፊቱ፤
ሆዳሙ እየሰባ፣ ጠርጎ በመብላቱ፣
ድሀው እየጫጫ፣ ሲቆጠር ጅማቱ፣
እንዳይስተካከል፣ከቱጃር በሞቱ፣
የዲታው ረዝሞ፣ በከበሮ ሲደምቅ፣
የጉዞ ፍታፍታቱ፣
የኔው ብጤው ፀሎት፣
ከመፍዘዙ እጥረቱ፣
በድፊያ ሲፈጸም፣ ግብዓተ መሬቱ፣
የማያይ መስሏቸው፣ ሠሪው ባለቤቱ፣
ዝም ብለው ካዩ፣ ቄሱ ነፍስ ኣባቱ፤
እንዳለ ከሆነ፣ለውጥ ካልታየበት፡
ላጣው ለገረጣው፣
ካፉ ላይ ነጥሎ፣ ቱጃር እየቀማው፣
ቢጣምን ቢደክም፣ አላልፍልህ ላለው፣
ላራሽ፣ ዋትቶ አደሩ፣
ሌላ ቀን፣ ምኑ ነው?
ቢቀርስ ቢምጣ፣ ሌላ ዓመት ምንድነው?
ባፍ-አደር ለፍላፊው፣
የ’ፖለቲካ’ው፣ ሰው፣
በዲሞክራሲም ሥም፣ ‘ተመርጦ በሥርዓት’፣
ማን አለብኝ ብሎም፣ ባምባ ገነንነት፣
ነፍጥ አንጋቢ ሽፍታ፣ የገባ በጉልበት፣
ሥልጣን ላይ ሲወጣ፣ ተኮፍሶ ባናት፣
ቡና እየተጣጣ፣ አንዱ ከሌላው ቤት፣
ጣል ግረፈው ካለ፣ ከልካይ ሳይኖርበት፣
ምንድነው እርባናው?
ወጡ ካልጣፈጠ፣ ካልተለየ ቃናው፣
እምን ላይ ነው ጥቅሙ፣ጉልቻ ቅየራው?
የናቴ ባል ሁሉ፣ አባትህ ነኝ ቢለኝ፣
እያወቀው ሆዴ፣ ተቀበል አትበሉኝ!
ከዝንጀሮ ቆንጆ፣ ላይኖር የሚመርጡት፣
ግራ ቀኝ ቢሉት፣
ከማህል ቢሰፍሩ፣ ከዳር ሆነው ቢያዩት፣
ምንድነው ፋይዳው?
ቢመረጥስ፣ ቢነግሥ፣በጉልበት ቢይዘው፣
ለውጡ የቱ ላይ ነው?
የናንተን አላውቅም፣ እኔ እንደማስበው፣
ሞኝ ሲያንጎራጉር፣ መላልሶ እንደሚለው፣
ያዲስ ዓመት ጉጉት ፡ያዲስ መሪ ተስፋው፣
አልበው የማይጠቱት፣ የሰማይ ላይ ላም ነው።
ምኞት ካልተሟላ ኑሮን ካልለወጠው፣
ቢመጣስ ቢቀርስ ሌላ ዓመት ምንድነው?
የዘንድሮው ዓመት፣ ላለም ለዘላለም፣
እንዳለ ቢወዘፍ እኔ ግድ የለኝም፤
መስከረም ሳይጠባ፣ ቀኑ ሳይለወጥ፣ በወና ጎጆዬ፣
ለሁልጊዜም ልኑር፣ ነገን ዛሬ ብዬ!

 

ሎንዶን፣ ግንቦት 2005 ዓመተ ምሕረት